Isaiah 51

የዘላለም ድነት ለጽዮን

1“እናንት ጽድቅን የምትከታተሉ፣
እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤
ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣
ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጕድጓድ ተመልከቱ።
2ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣
ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤
በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤
ባረክሁት፤ አበዛሁትም።
3 እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤
ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤
ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣
በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤
ተድላና ደስታ፣
ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በእርሷ ይገኛሉ።

4“ወገኔ ሆይ፤ አድምጠኝ፤
ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤
ሕግ ከእኔ ይወጣል፤
ፍርዴም ለሕዝቦች ብርሃን ይሆናል።
5ጽድቄ በፍጥነት እየቀረበ፣
ማዳኔም እየደረሰ ነው፤
ክንዴም ለመንግሥታት ፍትሕን ያመጣል፤
ደሴቶች ወደ እኔ ይመለከታሉ፤
ክንዴንም በተስፋ ይጠብቃሉ።
6ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፤
ወደ ታች ወደ ምድርም ተመልከቱ፤
ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፤
ምድር እንደ ልብስ ታረጃለች፤
ነዋሪዎቿም እንደ ዐሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፤
ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤
ጽድቄም መጨረሻ የለውም።

7“እናንት ጽድቅን የምታውቁ፣
ሕጌንም በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች ስሙኝ፤
ሰዎች ሲዘብቱባችሁ አትፍሩ፤
ሲሰድቧችሁ አትደንግጡ።
8ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋል፤
ትል እንደ በግ ጠጕር ይውጣቸዋል፤
ጽድቄ ግን ለዘላለም፣
ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንታ ትኖራለች።”

9 የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፤
ተነሥ፤ ተነሥ! ኀይልን ልበስ፤
እንዳለፉት ዘመናት፣
በጥንት ትውልዶችም እንደ ሆነው ሁሉ ተነሥ።
ረዓብን የቈራረጥህ፣
ታላቁን ዘንዶ የወጋህ አንተ አይደለህምን?
10የዳኑት እንዲሻገሩ ባሕሩን፣
የታላቁን ጥልቅ ውሆች ያደረቅህ፣
በጥልቁም ውስጥ መንገድ ያበጀህ፣
አንተ አይደለህምን?
11 እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤
በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤
የዘላለማዊ ደስታን አክሊል ይቀዳጃሉ፤
ተድላና ደስታ ያገኛሉ፤
ሐዘንና ልቅሶም ከእነርሱ ይሸሻል።

12“የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤
ሟች የሆኑትን ሰዎች፣
እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች
ለምን ትፈራለህ?
13የፈጠረህን፣
ሰማያትን የዘረጋውን፣
ምድርን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤
ሊያጠፋህ ከተዘጋጀው፣
ከጨቋኙ ቍጣ የተነሣ፣
በየቀኑ በሽብር ትኖራለህ፤
ታዲያ የጨቋኙ ቍጣ የት አለ?
14ዐንገታቸውን የደፉ እስረኞች በፍጥነት ነጻ ይወጣሉ፤
በታሰሩበትም ጕድጓድ ውስጥ አይሞቱም፤
እንጀራ አያጡም።
15ሞገዱ እንዲተምም ባሕሩን የማናውጥ፣
እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤
ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
16ቃሌን በአፍህ አኖርሁ፤
በእጄ ጥላ ጋረድሁህ፤
ሰማያትን በስፍራቸው ያስቀመጥሁ፣
ምድርን የመሠረትሁ፣
ጽዮንንም፣ ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’ ያልሁ እኔ ነኝ።”

የእግዚአብሔር የቍጣ ጽዋ

17 ከእግዚአብሔር እጅ፣
የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣
ዝቃጩ እንኳ ሳይቀር፣
ሰዎችን የሚያንገደግደውን ዋንጫ የጨለጥሽ፣
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤
ተነሺ፤ ተነሺ።
18ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣
የመራት አንድም አልነበረም፤
ካሳደገቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣
እጇን ይዞ የወሰዳት ማንም አልነበረም።
19እነሆ፤ በጥፋት ላይ ጥፋት መጥተውብሻል፤
ታዲያ ማን ያጽናናሻል?
እነርሱም መፈራረስና ጥፋት፣ ራብና ሰይፍ ናቸው፤
ታዲያ ማን ያስተዛዝንሽ
የሙት ባሕር ጥቅልሎች፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ የቩልጌትና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ ታዲያ እንዴት አስተዛዝንሻለሁ ይላል።
?
20ወንዶች ልጆችሽ ዝለዋል፤
በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ፣
በየጐዳናው አደባባይ ላይ ተኝተዋል።
የእግዚአብሔር ቍጣ፣
የአምላክሽም ተግሣጽ ሞልቶባቸዋል።

21ስለዚህ አንቺ የተጐዳሽ፣
ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ ይህን ስሚ።
22ሕዝቡን የሚታደግ አምላክሽ፣
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ ከእጅሽ፣
ያንገደገደሽን ጽዋ ወስጃለሁ፤
ያን ጽዋ፣ የቍጣዬን ዋንጫ፣
ዳግም አትጠጪውም፤
23ባስጨነቁሽ፣
‘በላይሽ ላይ እንድንሄድ ተነጠፊልን’
ባሉሽ እጅ ላይ አደርገዋለሁ፤
ጀርባሽን እንደ መሬት፣
እንደ መሸጋገሪያም መንገድ አደረግሽላቸው።”
Copyright information for AmhNASV